ተስፋ ማለት በእግዚአብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ ከስሜት የራቀ አላማውም እጅግ ፅኑ የሆነ የማይናወጥ እውነት ነው፡፡
አንዳንድ ግዜ በትክክል መተንፈስ እስኪያቅተኝ ድረስ ልቤ ደረቴን ፈንቅሎ የወጣ ሲመስለኝ፣ እየሆነ ያለውንና ሊሆን የሚችለውን በማሰብ በፍርሀት እና ጭንቀት ውስጥ ራሴን አገኘዋለሁ፡፡ሰውነቴ፣ አእምሮዬና ነፍሴ፤ ሁለንተናዬ ከሞት ጋር ግብግብ የፈጠሩ ያህል ይሰማኛል፡፡
በዚህ ጊዜ የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ባዶ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ለራሴም ነገሮች እንዳበቃላቸው፣ እነዚህ የጭንቅ ግዜያቶች እንደማያልፉና የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ሜዳላይ እንደቀሩ አስባለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር መጽናናት እራሴን አርቄ፤ አለማመንና ጥርጣሬ ሁለንተናዬን እንዲቆጣጠረው እፈቅድለታለው፡፡ ነገር ግን በግዜው ያልተረዳውት ነገር ቢኖር ተስፋ ማለት ስሜት እንዳልሆነ ነው፡፡ ይልቁንም ተስፋ ማለት ትክክል፤ ፈፁም፤ እና እውነተኛ በሆነው በእግዚአብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ እውነታ ነው፡፡
ተስፋ ግዜያዊ በሆነ ስሜት ላይ መሠረቱን አላደረገም፤ ይልቁንም እውነተኛ በሆነው በእግዚአብሄር ማንነት ላይ ነው የተመሰረተው፡፡
ሮሜ 5:5(አመት) “ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሷልና።”
እርሱ በድካማችን እንድንወድቅ የሚተወን አምላክ ስላልሆነ ተስፋችን የሚያሳፍር አይሆንም፡፡
ተስፋ የማይጨበጥ ምኞት አይደለም፡፡ ይልቁንም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን የሚፈስ ህያው የሆነ የእግዚአብሄር እውነት ነው፡፡ እኛ የምናምነው የእግዚአብሄር ባህሪ እርሱ ፍቅር እና ፍፁም የሆነውን ነው፡፡ ለዛም ነው በዚህ ተስፋ ልባችን የማይወርደው፡፡ ተስፋችን እጅግ ፅኑ የሆነና የተጠበቀ ነው፤ በማዕበል ውስጥ እንደሚይዘን መልህቅ እንዲሁም ደግሞ ከባድ በሆኑ የስሜት እና የሁኔታዎች ሞገድ ውስጥ እንዳንጣል የሚረዳን ነው፡፡ በክርስቶስ አማካኝነት የተቀበልነው ይህ ተስፋ ደካማ ሳይሆን በብዙ መናወጥ ውስጥ የሚፀና ነው፡፡
ዕብራውያን 6:19(አመት) “እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል።”
እግዚአብሄር ሁሉን ነገር እንደወደደና እንደፈቀደ በራሱ ግዜና ሰዓት ነው የሚሰራው፡፡ ነገሮች የዘገዩ ቢመስልም እርሱ ግን ሁሉን ነገር በግዜው ውብ አድርጎ ይሰራዋል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሄር ጊዜ ፍፁምና ትክክል ስለሆነ እርሱ በጊዜው የወደደውን ያደርጋል፡፡ እምነታችንን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በምናደርግበት ግዜ እነዛ ከባድ የሚመስሉ ግዜያቶች አስደናቂ ወደ ሆኑ ድሎች ይመሩናል፡፡ ከነዛ ከባድ ከሆኑ የጭንቅ ቀናቶች ውስጥ እግዚአብሄር ደስ የሚል የድልን ዜማ ይሰጠናል፡፡
ማንም ሊደርስልኝ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ለብቻዬ ሆኜ፤ የሚሰማኝ ሰው ካለብዬ ረዥም ግዜ አምብቻለሁ፡፡ ፈውስን እፈልግ ነበር፤ ነገር ግን በነዛ ከባድ ግዜዎች ዝም ያለኝ መስሎኝ ተሰማኝ፤ እንዲሰማኝ እንዴት ብዬ ላግኝው? ጌታ ሆይ የአንተን መልካምነት ሳልረዳ ቀርቼ ይሁን? ለምንድነው አንተን መጠበቅ አድካሚ መስሎኝ የተሰማኝ? ያንተን ቃል እየተጠራጠርኩኝ ይሁን? ለምንደነው ልቤ ወዳለማመን የሚያዘነብለው?(ኢሳያስ 55፡8-9) ጌታ ሆይ አንተን መስማት እችል ዘንድ በልቤ ውስጥ ያለውን አለማመን አስወግድልኝ፡፡ ያንተን ግዜ በመጠራጠር ውስጥ ሆኜ ከራሴ ጋር ብሟገት እንኳን፤ ያንተን ግዜ መጠበቅ ብዙ ትርፍ እንዳለው ልቤ ያውቃል፡፡(መክብብ 3፡11) በፈራሁ ግዜ እንኳን ለእኔ ቅርብ እንደሆንክ ነፍሴ ታውቅሀለች፡፡
አንዳንድ ግዜ የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት እንቸኩላለን፡፡ የምንፈልገውንም ነገር በመጠበቅ ውስጥ እንደክማለን፡፡ አንድ የተረዳውት ነገር ቢኖር ግን ከእግዚአብሄር የራቅሁና የተለየው በመሰለኝ ግዜ ይበልጥ ወደሱ መቅረቤ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል፤ የእኛ መንገድና ሀሳብ ከእግዚአብሄር የተለየ እንደሆነና የእርሱ ጊዜ ግን ፍፁም እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ለዛም ነው በእግዚአብሄር ቃል እና መልካምነቱ መደገፍ ያለብን፡፡ በእርሱ ላይ የምንታመን ከሆነ ሁለንተናችንን በሰላም ይሞላዋል፡፡ ጌታ ሆይ በነገሮች ላይ ልቤን ከመጣል ይልቅ አንተን እንዳውቅ እርዳኝ፡፡ ልቤ በአንት ላይ እንዲያርፍ አንተን ተስፋ ማድረን አብዛልኝ፡፡ አሜን፡፡
ሁለቱም የህይወቴ ገፅታዎቼ በውድቀት የተሞሉ ናቸው፡፡ ብቁ እንዳልሆንኩና ባዶ እንደሆንኩ ይሰማኛል። በዚህ ምክንያት ስለነገ ለምን ተስፋ አደርጋለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህ ነው በክርስቶስ ተስፋ ማድረግ የሚያስፈልገኝ፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ብዙ ግዜ ወድቄያለው ወደፊትም ደግሞ ልወድቅ እችላለው ስለዚህ በራሴ መተማመን ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሚያግዘኝ ላስብ ይገባል፡፡ ይህ የህይወት ትግል እጅግ ከባድ ቢሆንም እኔን ያዳነ እግዚአብሔር ታማኝ ስለሆነ ከከበቡኝ ሀዘኖች ይጠብቀኛል፡፡ ስለዚህም በእርሱ ውስጥ ሰላምን አገኛለው፡፡
ተስፋ ፍፁም ሊሆን የሚችለው ትክክለኛ ከሆነ ምንጭ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡ ለዛም ነው የተስፋችን መሠረቱ እግዚአብሄርና ቃሉ ብቻ ነው የምንለው፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው። ሰውን መከታ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል። ነፍሴ ሆይ፤ ዐርፈሽ እግዚአብሔርን ብቻ ጠብቂ፤ ተስፋዬ ከእርሱ ዘንድ ነውና። ዐለቴና መድኀኒቴ እርሱ ብቻ ነው፤ መጠጊያዬም እርሱ ነው፤ እኔም አልናወጥም። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል። እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። ኤርምያስ 17:7(አመት)መዝሙር 118:8-9(አመት)መዝሙር 62:5-6(አመት)ምሳሌ 3:5-6(አመት)ዕብራውያን 6:19(አመት)
ህይወት ሁልጊዜ መልካም ላይሆን ይችላል፤ በብዙ ፈተናና ችግሮች ውስጥ የምናልፍበት ጊዜ ይኖራል፡፡ ስለዚህ በዚህ እውነት ውስጥ ሆነን ነው ተስፋችንን የምናድሰው፡፡ ከሁሉ በላይ ግን፤ ከእግዚአብሔር የምናገኝው ነገር ሳይሆን መፈለግ ያለብን ራሱ እግዚአብሔርን ነው፡፡ የምንኖርበት አለም በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ራሳችንን ማሳረፍ ያለበን ፍፁም በሆነው በክርስቶስ ተስፋ ላይ ነው፡፡ እጅግ ተስፋ በሚያስቆርጥ የህይወት ትግል ውስጥ ብንሆን እንኳን እግዚአብሔር ለእኛ መልካም የሆነ አላማ አለው፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይመራናል፤ መልካም በሆነ ተስፋዎቹ ነፍሳችንን ያለመልማታል፤ ከሁሉ በላይ ግን ትልቁ ደስታችን የሆነው ሰላምና ፍቅር ባለበት ከእርሱ ጋር ለዘላለም የምንኖርበትን ቤት አዘጋጅቶልናል፡፡
[2] Streams in the Desert by L.B. Cowman.
[3] A Grief Observed by C.S. Lewis, Chapter 4.
[4]The-Power-of-Hope by Joyce meyer


